#የመሪነት_ደረጃዎን_ከፍ_ማድረግ_ይፈልጋሉ?
ሰዎችን ለማነሳሳትና በመሪነት ስኬትን ለማምጣት የሚረዱ አስር የውጤታማ መሪዎች ባህሪያትን ቀጥለን እንመልከት🚀
1. 👉#የጠራ_እይታ (Clear vision)
መሪ ተከታዮችን ወዴት እየመራ እንደሆነ የጠራ ዓላማና ግልፅ ራዕይ ከሌለው እየመራ ሳይሆን እያደናገረ ነው ልንል እንችላለን። መሪ ስለተሰጠው ኃላፊነትና ስለሚመራው ተቋም ግልፅ ርዕይ ያለው ሊሆን ይገባል። ይኼ ካልሆነ በተቋሙ ውስጥ ቀደም ሲል የነበረውን አሰራርና ተቋማዊ ባህል (status quo) ከማስቀጠል ውጪ ልዩነት የሚፈጥር አዲስ ነገር ይዞ መምጣት አይችልም።
2. 👉#ውጤታማ_ተግባቦት (Effective communication)
መሪ የሚያስበውን ሀሳብ ግልፅና አሻሚ ባልሆነ መንገድ ማስረዳትና ማሳመን የሚችል፣ ለተግባቦት ጠንቅ የሆኑ አሉታዊ ሀሳቦችንና ቃላትን የማይጠቀም፣ ለስራ የሚያነሳሳና የሚያበረታታ፣ ገንቢ ግብረ መልስ የሚሰጥ፣ ጥሩ አድማጭና ውጤታማ የተግባቦት ክህሎት ያለው ሊሆን ይገባል፡፡
3. 👉#ለዓላማ_ያለው_ታማኝነት (Integrity)
መሪ ከግል ፍላጎቱ ይልቅ የጋራ ዓላማን በማስቀደም ለሚመራቸው ሁሉ ጥሩ ምሳሌ መሆን መቻል አለበት፡፡ መሪው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንኳ እየመራ ያለ ቢሆን ሐቀኝነቱንና መልካም ምግባሩን መጣል የለበትም፡፡ ምክንያቱም ታማኝነት (integrity) ሲጎድል መሪነት ማብቅያው ይሆናልና፡፡
4. 👉#ሌሎችን_ማብቃት (Empowering others)
በሌሎች ውስጥ ያለውን እምቅ አቅም እንዲያወጡና እንዲጠቀሙ ማስቻል የመሪነት ተፅዕኖ መፍጠሪያ ዋነኛ መንገድ ነው፡፡ መሪዎች ተከታዮቻቸው የሚማሩበት፣ የሚያድጉበትና መሪነትን የሚለማመዱበት ምቹ ከባቢ (environment) በመፍጠር እውነተኛ ለውጥና እድገት እንዲመጣ ማድረግ አለበት፡፡
5. 👉#ውሳኔ_ሰጪነት (Decision making)
ሁኔታዎች በቅጽበት በሚለዋወጡበት፣ አጠራጣሪ ነገሮች በሞሉበት ዓለም ላይ ሳያወላውሉ ውሳኔ እየሰጡ መምራት የመሪውን ተፅዕኖ የመፍጠር ደረጃን ከፍ ያደርጋል፡፡ ውሳኔ የመስጠት እርምጃ በተሳታፊዎች ብቃት፣ በመረጃና በጊዜ ላይ ጥገኛ በመሆኑ ተገቢውን መረጃ በማጣራት አሳታፊና ወቅቱን የጠበቀ ውሳኔ መስጠት መቻል ከመሪዎች የሚጠበቅ ነው፡፡
6. 👉#ስሜትን_መገንዘብ (Emotional awareness)
መሪ ከሌሎች አብሮ ሰራተኞች አንዱ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ በመሆኑም የሌሎችን ህመም አይቶ ባላየ የሚያልፍ ሳይሆን ለሌላው ደህንነት የሚያስብ፣ የሚሰማቸውን ስሜት እንዲያንፀባርቁ እድል የሚሰጥ፣ በሀዘንም ሆነ በደስታ ከተከታዮች ጎን የሚቆም፣ ስሜታቸውን የሚረዳ ሊሆን ይገባል፡፡
7. 👉#ኃላፊነት_መውሰድ (Taking responsibility)
እውነተኛ መሪዎች ለግል ስህተታቸውም ሆነ ለቡድኑ ውድቀት ኃላፊነት የሚወስዱ እንጂ የሚሸሹ አይደለም፡፡ ግልፅ የሆኑ የአፈጻጸም ግቦችን (performance expectations) በማስቀመጥ ሰዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያበረታታቸዋል፡፡ ተከታታይ መሻሻልና የአፈፃፀም ብልጫ እንዲኖር በተጠያቂነት መንፈስ ይንቀሳቀሳል፡፡ ኃላፊነትን የሚወስድ መሪ ስኬት ሲኖር "የእኔ" ስህተት ሲኖር "የእነሱ" የሚል አይደለም።
8. 👉#ለውጥን_መላመድ (Adapting to change)
በዓለም ላይ የማይቀር ብቸኛ ቋሚ ነገር ለውጥ ነው፡፡ ለለውጥ ያልተዘጋጀ መሪ ከጊዜው ጋር አብሮ መጓዝ አይችልም፡፡ ሁኔታዎች ሲቀየሩ ከሁኔታዎች ጋር አብሮ የሚሄዱ ስልቶችን መንደፍ፣ ፈተናዎችንና ውድቀቶችን እንደ መማሪያ እድሎች የሚወስድ መሪ ውጤታማ ሆኖ የሚቀጥል ነው፡፡
9. 👉#የቡድን_መንፈስ_መገንባት (Building team spirit)
የተባበረና የተነቃቃ ቡድን መገንባት ያልቻለ መሪ ወደፊት ለመጓዝ እግሩ ይያዛል፡፡ መሪ የቡድኑን የጋራ ማንነት፣ ጓዳዊነትን በማጠናከር እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ የሆነ ቡድን መገንባት አስፈላጊ ነው፡፡ ትልቅም ሆነ ትንሽ የተገኙ ድሎችን በጋራ የማክበርና የመመሰጋገን ባህልን ማጠናከር መሪው የቡድን መንፈስን ለመፍጠር ያግዛል፡፡
10. 👉#ግጭቶችን_መፍታት (Conflict resolution)
ውጤታማ መሪዎች ግጭቶችን የሚያስወግዱ ሳይሆን ውጤታማ በሆነ መንገድ የቡድኑን አንድነት ሳይረብሽ እንዲፈታ መንገድ የሚቀይሱ ናቸው፡፡ የችግሮችን ምልክቶች ለማጥፋት ብቻ ሳይሆን ዋናውን መንስኤ የሚፈታ ዘላቂ መብትሔ በማፈላለግ ላይ ያተኩራሉ፡፡
እነዚህን ከላይ የተጠቀሱ አስር ባህሪያትን የራሱ ያደረገ መሪ በመሪነት ደረጃው ከፍ ያለ ተፅዕኖ የማያሳድርበትና ለውጥ የማያመጣበት ምክንያት አይኖርም፡፡ የእርስዎን አመራር ሂደት በደንብ ይፈትሹና ለማስተካከል ይሞክሩ፡፡