እያንዳንዱ የምንሠራው ሥራ ከዕለት ጉርስ ማግኛነት ባለፈ የውስጣችንን ማንነት፣ ትዕግሥት እና የጥበብ ጥማት የምናሳይበት ትልቅ መድረክ ነው ብዬ አምናለሁ። ለእኔ ሥራ ማለት እንዲሁ ዝም ብሎ የሚከናወን ሜካኒካዊ ተግባር ሳይሆን፣ ከአእምሮ ፍልስፍና ተነሥቶ በእጆች የሚቀረጽ ሕያው ጥበብ ነው።
በተለይ በእንጨት ሥራና በዕደ-ጥበብ (Art & Crafts) ዓለም ውስጥ ስንቀሳቀስ ሥራን ከሕይወት ፍልስፍና ጋር የማገናኝባቸው ሦስት ዋና መርሆዎች አሉኝ፦
1. ትዕግሥት እና ጥንቃቄ (Patience & Precision)
አንድን ሸካራ እንጨት አልምዶ፣ መልክ አስይዞና ጥራት ባለው መልኩ አውጥቶ ለዓይን የሚማርክ የብርሃንና የውበት መገለጫ ማድረግ የሚቻለው በትዕግሥት ብቻ ነው። ሕይወትም ልክ እንደዚሁ ናት፤ ጥሬ ዕቃዋን በትዕግሥትና በጥንቃቄ ካልቀረጽነው የምንፈልገውን ውብ ውጤት አናገኝበትም።
2. የፈጠራ ነጻነት (Creative Freedom)
ጥበብ ካለፈው ልምድ እየተነሣች አዲስ ዕይታን የምትፈጥር ነፍስ ናት። በምሠራቸው የእጅ ሥራዎች ሁሉ ውስጥ "የፊኒሽንንግ ሥራዎችንና የእንጨት ሥራዎችን" አንዳንዴ ደግሞ "የቀይብዕር ዲያሪ" በተሰኘ ማህበራዊ ሚዲያ ጥልቅ የጥበብ እና የእውቀት ማረፊያ ሐሳብ ለማንጸባረቅ እጥራለሁ። እያንዳንዱ የተጠናቀቀ ሥራ የራሱ የሆነ ታሪክና ፍልስፍና እንዲኖረው ማድረግ የዘወትር ፍላጎቴ ነው።
3. ታማኝነትና ጥራት (Integrity & Excellence)
የእጅ ጥበብ ሥራ ትልቁ መለኪያው ከውስጥ የሚመነጭ ታማኝነት ነው። ሰው ቢያየውም ባያየውም፣ ከውስጥ የሚደረገው ጥንቃቄና ለሥራው የሚሰጠው ክብር የውጤቱን ጥራት ይወስነዋል። የምንሠራው ሥራ የእኛ መስታወት ነው።
ይህ "ሥራና ፍልስፍና" የተሰኘው ክፍል፣ በሥራዎቻችን ውስጥ የምናሳየውን ጥረት፣ የምንቀስመውን እውቀት እና የሕይወትን ጉዞ የምንመረምርበት የጋራ መወያያ መድረካችን ይሆናል።
የእናንተስ የሥራ ፍልስፍና ምንድን ነው? በዕለት ተዕለት ሥራችሁ ላይ ትልቁ መመሪያችሁ ምንድን ነው? አሳቡን በኮሜንት አጋሩኝ!